Monday, April 8, 2013

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (1)


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
       በ2005ዓ.ም ዘመነ ማቴዎስ ቅዱስ እግዚአብሔር ባዘጋጀልን ጉባኤ መንፈስ ቅዱስ በገለጠልን መጠን ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መማር እንጀምራለን፡
ትምህርቱ የሚዳስሳቸዉ ነጥቦች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ
·         ቀዳማዊ ወድኅራዊ ሕያዉ ዘላለማዊ አምላክ ስለመሆኑ
·         ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት ስለመወለዱ(ስለ ሁለቱ ልደታት)
·         ስለ ድንቅ  ልደቱና የልጅነት ህይወቱ፣ ስለጥምቀቱ፣ ስለትምህርቱና፣ ስለተዓምራቱ፣ ስለህማሙ፣ስቅለቱ፣ ሞቱ፣ትንሣኤዉና ዕርገቱ፣ዳግመኛም ለፍርድ ስለመምጣቱ፣ ወዘተ…ይሆናል፡፡

       በቅድሚያ አንድን አካል "አምላክ" ነው ለማለት የአምላክነት ባህርያት ምን እንደሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የሁሉ ነገር የማንነቱ መገለጫ ወሰን ባህርዩ ነውና፡፡ ሰለዚህ የአምላክነት ባህርያት የሚባሉትና የየትኛዉንም ሃይማኖት ተከታይ ወይም ፍልስፍና አራማጅ የሚያስማሙት፡-
-    ሕያዉነት(ዘላለማዊነት)    - ሁሉን ቻይነት(Omnipotent)   - ሁሉን አዋቂነት (Omniscient)
-    በሁሉ ስፍራ መገኘት(በቦታ አለመወሰን)Omnipresent
-    ተወካፌ ጸሎት ወአኮቴት (የፍጡራንን ሁሉ ጸሎትና ምስጋና ለመቀበል የተገባው)
-    ዘሥሉጥ ላዕለ ኵሉ(በሁሉ ላይ የሠለጠነ፡በዋናነት ሊጠቀሱ የሚገባቸው ናቸው፡፡

1.   ሕያውንት(ዘላለማዊነት):- የዘላለማዊነት ጫፍ ከመገኘት በኋላ (ድኅረ ህላዌ) የሚመጣ ብቻ ሳይሆን ከፊትም የሚኖር ነው' የዘላለም ጫፍ ፊተኛ እና ኋለኛ መሆን ማለት ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ቅዱስ እግዚአብሔርን የሚመስለው የለም "ኣልቦቱ ጥንተ ወኢተፍፃሜት" እንዲል በቀዳማዊነት ባይሆንም በድህራዊነት ግን ሰውና መላዕክት ይመስሉታል፡፡

     ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን በሰው ምሳሌ ሆኖ የባርያውን መልክ ይዞ በመካከላችን ቢገለጥም እርሱ ዘላለማዊ ህያው አምላክ መሆኑን ከዚህ በታች የተጠቀስት ምንባባት ያስረዳሉ፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች

v  መዝ109(110) *3 :- ከአንተ ጋር ቀድሞ በኃይልህ ቀኝ በቅዱሳን ብርሃን ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ          ከሆድ ወለድሁህ
v  ምሳ 8 *2-36:- "…እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመርያ አደረገኝ በቀድሞ ሥራዉ መጀመሪያ@ ከጥንቱ ከዘላላም  ጀምሮ ተሾምሁ ምድር ከመፈጠርም አስቀድሞ ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፡፡
v  ትን.ኢሳ 48*16:- "…ወደ እኔ ቅርቡ ይህንም ስሙ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስዉር አልተናገርሁም ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል"
v  ትን.ሚክ 5* 2:- "አንቺም ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንደ ታናሽ ነሽ  ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል፡፡ (ከማቴ 2፤5-6 ጋር ይገናዘብ)
v  ዮሐ 1*1-3 :- "በመጀመርያ ቃል ነበር ቃልም በእግዚአበሔር ዘንድ ነበር ቃልም እግዚአብሔር ነበር…ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳንች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም"
v  ዮሐ 1*30 :- "አንድ ሰው ከኃላዬ ይመጣል ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኗል" መጥምቁ ዮሐንስ ጌታን በሥጋ ልደት 6 ወር እንደሚቀድመዉ በግልፅ የታወቀ ሲሆን እንዴት እንዲህ አለ ቢሉ በቅድምና መኖሩን ማኅፀነ ማርያም የህላዌው መጀመርያ መገኛ አለመሆኑን ለማመልከት ነው፡፡
v  ዮሐ 8* 55-59 :- "… ገና ሃምሳ አመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት ኢየሱስም እዉነት እውነት እላችኋለሁ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ" አላቸዉ፡፡
v  ዩሐ17* 5 :- "… አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንደ በነበረኝ ክብር አክብረኝ
v  ዕብ1*10:- "… ስለ ልጁ ግን ጌታ ሆይ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ እንደ መጎናፀፍያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጠማል@ አንተ ግን አንተ ነህ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም" ቅዱስ ጳዉሎስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት አንዱ ለመሰላቸው እርሱ የመላእክት ጌታ አምላክ እንጂ መልዐክ አለመሆኑን ሲያስረዳ የፃፈው ነው፡፡
v  ራዕ5* 6-8:- "…እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል ዓይንም ሁሉ የወጉትን ያዩታል… ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል፡፡
v  ራዕይ 1*17-18:- "… አትፍራ ፊተኛዉና መጨረሻዉ ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያዉ ነኝ"፡፡
v  ራዕይ 22*12:- "… እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራዉ መጠን እከፍል ዘንድ ወጋዬ ከአኔ ጋር አለ አልፋና ዖሜጋ ፊተኛዉና ኃለኛው መጀመሪያዉና መጨረሻው እኔ ነኝ"፡፡

ተጨማሪ ጥቅሶች:- ሉቃ 1* 31-36 & ዮሐ 10* 30& ዮሐ14* 8-11& ቈላ 1*15-20


ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ቀሲስ ታምራት ውቤ
መስከረም 2005 ዓ.ም





                                                                                                                                                                                





በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
          ባለፈዉ ትምህርታችን የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አልፋና ዖሜጋ ፊተኛዉና ኃለኛው ከዘላለም እስከ ዘላለም ህያው የሆነ አምላክ መሆኑን በተረዳ ነገር አይተናል' በይቀጥላል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ያለውን እውነታ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ እናያለን፡፡
ሁሉን ቻይ :- ማለት እንዳሰበ የሚሠራ እንደፈቀደም የሚያከናዉን& ለሥራው ረዳት አጋዥ    አማካሪ የማይሻ& ሁሉን ከባህርይ የሚያከናውን& በሰማይም ሆነ በምድር ከምድርም በታች በሁሉ የሚሠራ& በሁሉ የሚያዝ በሁሉ ላይ የሠለጠነ &ማንም ማን ለምን ይህን ታደርጋለህ ብሎ ሊከለክለዉ ሊያግደው ሊያስቆመው የማይቻል& በአጠቃላይ ይበልጥ ገላጭ በሆነ ቃል "የሚሳነው ነገር የሌለ" ማለት ነው፡፡ ጥያቄዉ ሁሉን ቻይ የሚለው የአምላካዊ ባህርይ መገላጫ ቅፅል ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ይገባዋል ወይ? የሚል ነው፡፡ የኦርቶደክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም መልስ እንዴታ ይገባል ነው!!!
ማስረጃ
ትን.ኢሳ 9*6 ህፃን ተወልዶልናልና……ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም አባት                  የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡ ኃያል አምላክ የሚለው ቃል የተወለደው በሥጋ የተገለጠው እርሱ ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን የሚያስረግጥ ነው፡፡
ዮሐ 1*3 ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም፡፡
          በዚህ ቃልም በቅደምና የነበረው ቃል በኋለኛው ዘመን ሥጋን የተዋሃደው ቃል ሁሉን የፈጠረ ሁሉን ያስገኘ ምንም ምን ያለእርሱ የሆነ እንደሌለ የሚያስረዳ ነው፡፡
ቆላ 1*15 እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው የሚታዩትንና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው፡፡ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሯል እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፡፡
የማይታ አምላክ ምላሌ ሲል አምላክ አይደለም ማለቱ አይደለም፡፡ "በሰው ምሳሌ ሆኖ" ሲል ሰው አልሆነም ለማለት እንዳለሆነ ሁሉ ፊል 2*6-8 ሁሉ በእርሱ እንደተገኘ ለእርሱ ክብርም እንደተፈጠረ በመግለጥ ሁሉን ቻይነቱን መሠከረ፡፡
      ፅንስቱ ሁሉን ቻይነቱን ሲያስረዳ
           ምድር ያለ ዘር ሴት ያለወንድ ትፀንስ ዘንድ ሕገ-ተፈጥሮ አይፍቅድም፡፡ ሁሉ የተገኝ በዚሁ የተፈጥሮ ሥርዓት አልፎ ነው፡፡ የጌታ ፅንት ግን እንዲህ አይደለም ወንጌላዊው ማቴዎስ" ለዮሴፍ ታጭታ ሳለች ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች" እንዳለ የጌታ ፅንስ ከሦስት ግብራት ንፁህ ነው፡፡ ይኸውም ዘር&ሩካቤ&ሰስሎተ ድንግልና ነው፡፡ጌታችን ሲፀነስ ሩካቤ አልተፈፀም፡ዘርዐ ብእሲ አላስፈለገም የእመቤታችን ድንግልናም አልተለወጠም፡፡ በዚህ እውነትም የተወለደልን ህፃን ኃያል አምላክ ወይም ሁሉን ቻይ መሆኑን ገለጠልን፡፡ 
     ማቴ 1*18-25 & ሉቃ 1*26-56
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደቱ ሁሉን ቻይነቱን ሲያስረዳ
      የጌታ ልደቱ እንደ ፅንሠቱ ሁሉ ልዩ ነው በልደቱ የእናቱን ድንግልና አልለወጠውም ምጥ ጭንቅ አላገኛትም፡፡ ሰው በር ከፍቶ ወጥቶ ከኋላዉ እንዲዘጋዉ የእርሱ ልደት እንዲህ አይደለም ማኅተመ ድንግልናዋ ለቅፅበተ ዓይን እንኳን አልተለወጠም ይህ እንዴት ይሆናል? ለሚል
-ጌታ በተዘጋ ቤት ጣርያ ሳይነቅል ግድግዳ ሳያፈርስ መሠረት ሳየቆፍር በር መስኮት ሳይከፍት እንዴት ከሐዋርያት መካከል እንደተገኘ ይመርምር፡፡ ሉቃ 24
ትን.ሕዝ 44*1-3 ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አምጣኝ ተዘግቶም ነበር እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል፡፡
             ምሥራቅ እመቤታችን የእውነተኛዉ ፀሐይ መውጫ ናትና& መቅደሰ የማኅፀንዋ 9ወር ከ5ቀን ተመስግኖበታልና& በር የማኅተመ ድንግልናዋ ተዘግቶ ይኖራል ማለቱ ለዘላለም እናትነትን ከድንግልና አስተባብራ ፀንታ መኖርሯን ሲገልጥ ነው፡፡
መዝ.ዳዊ 146*1-2 ኢየሩሳሌም ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኚ ጽዮንም ሆይ ለአምላክሽ እልል በይ የደጆችሽን መወርመርያ አፅንቷልና፡፡ /በዚህ ጥቀስ ኢየሩሳሌም ጽዮን የተባለች እመቤታችን የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና& የደጆችሽ መወርወርያ የተባለ ማኀተመ ድንግልናዋ ነው አፅንቶ እንደሚጠብቀው ግልጽ ሆኗል፡፡
ኢሳ 66*7 ሳታምጥ ወለደች* ምጥም ሳያገኛት ወንድ ልጀን ወለደች ከቶ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? እንዲህ ያለ ነገርስ ማን አይቶአል?
የህፃንነት እድሜው
           በተዐምረ ኢየሱስና በተለያዩ የቤ/ክ መፃህፍት እንደተገለጠው ጌታ በህፃንነቱ ይፈፅማቸው የነበሩ ተዐምራቶች ሁሉን ቻይ አምላክ ለመሆኑ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስም ከሩቅ ምሥራቅ የመጡትን የጥበብ ሰዋች በኮከብ መምራቱ ሊቃውንትን በሚጠይቀው ጥያቄና በሚሠጠው መልስ ማስደመሙ በተፈጥሮ ላይ ያለውን ሥልጣን እውቀቱም የባህርይ መሆኑን ያስረዳል፡፡
ይቆየን!
                                    ወስብሐት ለእግዚአብሔር                                  ቀሲስ ታምራት ውቤ
                                    ጥቅምት 2005ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
         በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
            በቀደመ ጽሑፋችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን ድንቅ በሆነ ጽንሰቱ፣ ልደቱና በልጅነት ወራት አስደናቂ ህይወቱ ተመልክተናል፡፡ በይቀጥላል ጌታችን በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቆ ራሱን በትምርቱና በተዐምራቱ በገለጠበት ወቅት የህንኑ አስረግጧል፡፡
ዮሐ 2፥1-12 ፡- በተገለጠው ተዐምራት ጌታችን ውሃውን ወደ ወይን መቀየሩን እናውቃለን፡፡ የውሃ እና የወይን ባህርይ በውስጣቸውም የሚይዙት ውሁድ(Substance) የተለያየ እንደሆነ የተረዳ ነገር ነው፡፡ ጌታ በዚህ ተዐምራቱ ካልነበረ(ከሌለ) ነገር አንድን ነገር ማምጣት(መፍጠር) የሚችል መሆኑን አሳይቶናል፡፡
ዮሐ 5፥1 ፡- 38ዓመት ልምሾ ሆኖ እንደትኋን ካልጋ ተጣብቆ የኖረውን መፃጉዕ በቃሉ ብቻ    መፈወሱ ሁሉን ቻይነቱን ያስረዳል፡፡
ዮሐ 9፥1 ፡- በደረቅ ግንባር ላይ ዓይን መፍጠሩም እንደዚያው በዚሁ ምንባብ ላይ ዓይኑ  የበራለት ሰው በሰጠው ምስክርነት "…ዓለም ከተፈጠረ የዕውርን ዓይን የከፈተ ከቶ አልተሰማም" ማለቱ የጌታችንን ሁሉን ቻይነት የሚያስገነዝብ ምስክርነት ነው፡፡
ማቴ 9፥27-31 ፡- ባለው ተመሳሳይ ታሪክም ሁለቱ ማየት የተሳናቸው ሰዎች እነዲምራቸው  ሲለምኑት "ይህን ማድረግ እንድችል ታምናለችሁ?" ብሎ ነበር የጠየቃቸው ሁሉን ማድረግ ከሚችል ከእርሱ በቀር በሥልጣን ይህን መናገር የሚችል ይኖራልን?
ሉቃ 13፥10-17 ፡- 18 ዓመት በድካም መንፈስ ጎብጣ የኖረች ሴት ሌሎችም በዚህ ጹሑፍ ያልተጠቀሱ ተዐምራቶች የሁሉን ቻይነቱ ማስረጃዎች ናቸው ወንጌል ይህን በአንድ ቃል ሲያጠቀልለው "ህሙማንን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡለት እርሱም ፈወሳቸው" ይላል ከመጣው ውስጥ ተስኖት ሳይፈውሰው የመለሰው አንድ ስንኳ የለም፡፡
በተፈጥሮ ላይ ሁሉን ቻይነቱን ሲገልፅ
ሉቃ 5፥1-10 ፡- ስምዖን ጴጥሮስና ጓደኞቹ ዓሣ ማጥመድ ሌሊቱን ሙሉ ሞክረው ተስኗቸው   ቀርተዋል፡፡ ጌታ ወደ ታንኳይቱ ገብቶ መረባቸውን በታንኳይቱ በስተቀኝ እንዲጥሉ ሲያዝ ሌሊቱን ደክመው መያዝ እንዳልቻሉ እንደቃሉ ግን መረቡን እንደሚጥሉ ገልፀው ቢጥሉ መረባቸው እስኪቀደድ ዓሣ ማጥመድ ችለዋል ይህም በተፈጥሮ ላይ ያለውን ኃይል ያሳያል፡፡
ማቴ 8፥22-25 ፡- ሐዋርያት የሚቀዝፉትና ጌታ ከበስተኋላ ያንቀላፋባት ታንኳ በብርቱ ማዕበል ስትንገላታ ባህሩም ሊደፍናት ሲቀርብ ሐዋርያት ጌታን ቀስቅሰው "ስንጠፋ አይገድህምን?" ባሉት ጊዜ ጌታ የእምነታቸውን ማነስ ወቅሶ ነፋሱን እና ማዕበሉን ገሠፀ ታላቅ ጸጥታም ሆነ ሐዋርያትም ሁሉን ቻይነቱን በተረዱ ወቅት "ነፋሳትና ባህር ስንኳ የሚታዘዙለት እርሱ ማንው? ብለው ሰገዱለት ይህም በተፈጥሮ ላይ ያለውን አዛዥነት በግልፅ ያስረዳል፡፡
ማቴ 14 ፡-በዚህ ሁለት ታላላቅ ተዐምራት ተደርገዋል፡፡ የመጀመርያው በአምስት ቂጣና በሁለት ዓሣ አምስት ሺህ ያህል ወንዶች ሴቶችን ህፃናት ሳይቆጠሩ መግቦ 12 ቅርጫት ፍርፋሪ ማስነሳቱ ሲሆን ሁለተኛው ሐዋርያት በባህሩ መካከል ሳሉ ባህሩን እነደየብስ እየረገጠ መምጣቱ፤ ጴጥሮስ ተጠራጥሮ ሊሰጥም ሲል በውሃ ላይ ቆሞ ውሃ ውስጥ የሚሰጥምን ማውጣቱ ለሁሉን ቻይነቱ መጋለጫ አይደለምን?
          እኒህ ከላይ የተገለፁት ተዐምራት ሁሉ ከአእምሮ በላይ የሆኑ ቢሆኑም ለሰው ልጅ በተሰጠው ደካማ ቋንቋ ስለተፃፉ ግን ውጣቸውን በመንፈስ ለመመርመርና ለማድነቅ ካልተዘጋጀን የሚፈጥሩብን ስሜትም እንዲሁ ደካማ ነው፡፡ በእምነት ለማደግ በቅዱስ እግዚአብሔር ፀጋ ለመበልፀግ ለሚጋደሉ ግን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ዓለማትን የፈጠረና ሁሉ በእርሱ ትዕዛዝ የሚመራ መሆኑን ለመረዳት ታሪኮቹ ከበቂ በላይ የሆኑ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ባነበብነው መልዕክት ጌታ መንፈስ ቅዱስ ህሊናችንን ለእውነታ ምርኮ ልቦናችንን  ለፍፁም አምልኮ የተዘጋጀ እንዲሆን ይርዳን!
ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ቀሲስ ታምራት ውቤ
ጥቅምት 2005

No comments:

Post a Comment